The Letter from Ethiopian Prison / የናትናኤል መኮንን ደብዳቤ ከቃሊቲ እስር ቤት

The Letter from Ethiopian Prison / የናትናኤል መኮንን ደብዳቤ ከቃሊቲ እስር ቤት

Mymmar

Myanmar is moving!
San Suu Kyiswon won ( even if it is a half-way on the way to Freedom & Democracy) the election after 20 Years of Peaceful Struggle.
Ethiopian prisons are still full of political prisoners after 20 Years of Tyranny; paradoxically supported by US and Western Europe;  the supposedly champions of Democracy and Peace!
Here is one of the letters from a young Ethiopian Political Prisoner – Mr. Natnael Mekonnen, accused of “Terrorism” – a catchword to silence all political opposition-; an outstanding and courageous plädoyer of a non-viiolent struggle for Peace and Democracy !
Freedom to all Political Prisoners !!!

*

ይድረስ ለክቡር ፍ/ቤት፤ ይድረስ ለኢትዮጵያ ህዝብ (1

ክቡር ፍ/ቤት ከመታሰሬ በፊት በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ድርጅቶች አባሎችን ማሰር የአቶ መለስ የ20 ዓመታት አገዛዝ የባህሪ መገለጫ በመሆኑ በማናቸውም ጊዜ ልታሰር እንደምችል የጠበቅኩ ቢሆንም እንደዚህ ዓይን ባወጣ ሁኔታ ከሽብር ጋር በተያያዘ እከሰሳለሁ ብዬ በህልሜም በውኔም አልጠበቅኩም ነበር፡፡ ምክንያቱም ትግሉ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት በድርጅቴ የውስጥ ስብሰባዎችም ሆነ ድርጅቱ ከህዝብ ጋር በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ወይም ደግሞ በግል ከግለሰቦች ጋር በነበሩኝ ውይይቶች ሁሉ በምሰነዝራቸው ሀሳቦችም ሆነ በምይዛቸው አቋሞች አገዛዙን በሰላማዊ መንገድ ታግሎ መለወጥ አማራጭ ብቻ ሳይሆን እምነታችንም መሆን እንዳለበት በተደጋጋሚ እገልፅ ስለነበርና በተግባራዊ እንቅሰቃሴዬም ከዚህ የተለዬ ተግባር ስላልነበረኝ ነው፡፡
ክቡር ፍ/ቤት በእኔ እምነት ሰላማዊ ትግል ሳትገድል የምትሞትበት ወንጀል ሳትሰራ በተደጋጋሚ የምትከሰስበትና ወደ ወህኒ የምትወርድበት እየተበደልክ ይቅር የምትልበት፣ በአጠቃላይ የሰውን መብት ለመንጠቅ ሳይሆን የራስን መብት አሳልፎ ላለመስጠት በፅናትና በታላቅ ዲስፕሊን የሚደረግ ሰላማዊ ተጋድሎ ነው፡ ፡ መጨረሻውም ቂምና በቀል ሳይሆን ፍቅርና እርቅ ነው፡፡
ክቡር ፍ/ቤት ከላይ የዘረዘርኳቸው የሰላማዊ ትግል መርሆዎች በመርህ ደረጃ ብቻ የማራምዳቸው ሳይሆኑ በዕለት ከእለት የትግል እንቅስቃሴዬ ውስጥም የተግባር መመሪያዎች ነበሩ፡፡ ስለሆነም በሽብር ተጠርጥረሃል ስባል የራሴን ማንነት ሳይሆን የተጠራጠርኩት አገዛዙ ምን ያህል ሰላማዊ ትግል የሚያካሂዱ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ከፖለቲካ መድረኩ ጠራርጐ ለማጥፋት እንደተዘጋጀና የህዝቡን ህገ-መንግስታዊ የነፃነትና የዴሞክራሲ ትግል ለማዳፈን ምን ያህል እንደቆረጠ የሚያሳይ ነው፡፡
ክቡር ፍ/ቤት፡- እኔ እንኳን ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር ስለመግደል ላሴርና የህዝብ ሀብት፣ የሆኑትን መሰረተ ልማቶች ስለማውደም ላቅድ ቀርቶ አፈናን፣ ጭቆናንና ግፍን በሰላማዊ መንገድ ከመታገልና ከመቃወም ውጭ የገዥውን ፓርቲ አባላትና አመራሮች እንኳን በጥላቻ ዓይን ተመልክቼ አላውቅም፡፡ ወደፊትም አልመለከታቸውም፡፡ ነገር ግን በፅናት አምርሬ እታገላቸዋለሁ፡፡ አፈናቸውን እንዲያቆሙ ከቁልቁለት ጉዟቸው እንዲመለሱ፤ ክቡር ፍ/ቤት፡- ሽብር የእኔ መገለጫ አይደለም፡፡ ሽብር የፓርቲዬ የአንድነት መገለጫ አይደለም፡፡ ሽብር የኢትዮጵያ ወጣት መገለጫ አይደለም፡፡ በአጠቃይ ሽብር የኢትዮጵያ ህዝብ መገለጫ አይደለም፡፡ እኔ የምለው አቶ መለስ የሽብር ህጉን በዓለም ምርጥ ተሞክሮ ካላቸው ሀገሮች ኮማ እንኳ ሳይቀር ቀድተው እንዳመጡት ነግረውናል፡ ፡ ነገር ግን አይደለም የሚፈነዳ ቦንብና ተተኳሽ ጥይት ሊይዙ ቀርቶ ስለሽብር የሚያወራ ወረቀት እንኳ ይዘው ያልተገኙ ሰላማዊ ፖለቲከኞችን አሸባሪ ብሎ ማሰርን ከየትኛው ሀገር ምርጥ ተሞክሮ ነው የቀዱት? መቼም የፖለቲካ ተቀናቃኝን በሽብር የመክሰስ ሴራ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ወይም የሽብር ህጉን በቀጥታ ከቀዱባቸው ሀገሮች እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በዓለም ላይ ከአቶ መለስ አገዛዝ በስተቀር በፖለቲካ የሚቀናቀኑትን ሰላማዊ ታጋዮች ሽብርተኛ ብሎ የከሰሰም ሆነ የፈረደ ሀገር የለም፡፡
ክቡር ፍ/ቤት፡- አገዛዙ እንዳለው እኔ ባለስልጣናትን ለመግደልና የህዝብ ሀብት የሆኑትን መሰረተ ልማቶች ለማውደም ያሴርኩ፣ ያቀድኩና በሽብር የተፈረጀ ድርጅት አባል ያልሆንኩና ከኢትዮጵያ ጋር በጦርነት ሁኔታ ላይ ካለው የሻዕቢያ መንግስት ጋርም የተባበርኩ ሳልሆን በሰላማዊ መንገድ የሚታገለው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ መስራችና የም/ቤት አባል ለአንድነት አላማዎች ተፈፃሚነት በቁርጠኝነት የምታገል፣ እንኳን ከሻዕቢያ ጋር ልተባበር፡- ከሻዕቢያ ጋር በመተባበር ሀገሬን የባህር በር ያሳጣትን አቶ መለስን ጭምር የምታገል ለሀገር አንድነትና ክብር የምታገል፣ ሀገር ወዳድ ዜጋ ነኝ፡፡
ክቡር ፍ/ቤት የድርጅቴም ዓላማ ሁላችንም በእኩልነትና በነፃነት የምንኖርባት ሀገር መፍጠር፣ ነፃነታቸውና ገለልተኝነታቸው የተረጋገጠ የፍትህ ስርዓት፣ የፀጥታ ኃይልና ሚዲያ መፍጠር፣ የህዝብን እኩል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተቋማዊ ሙስናን ማስወገድ፣ ህዝብ የሚፈራቸው ሳይሆን ህዝብን የሚያከብርና ተጠያቂነት ያለው መንግስት መመስረት፣ ዘረኝነትና አድሏዊነትን መዋጋትና ብሔራዊ መንግስትና ብሔራዊ እርቅ እንዲፈጠር መታገል ናቸው፡፡
ክቡር ፍ/ቤት፡- በእኔም ሆነ በድርጅቴ በአንድነት እምነት አሁን በስልጣን ላይ ያለው ሥርዓት ከሻዕቢያ ጋር በመተባበር ደርግን ከስልጣን አስወገደ እንጂ ዴሞክራሲን አላመጣልንም፡፡ ጭቆናን አላስወገደልንም፡፡ እነ አሞራው ሞቱለት የተባለው የ17 ዓመታት የእኩልነትና የዴሞክራሲ ትግል እነሱ የታሰሩበት የምርመራ ክፍል እንኳን ሳይቀር እኔን ጨምሮ ሰላማዊ የዴሞክራሲና የነፃነት ታጋዮች በግርፋት ቁም ስቅላቸውን አይተውበታል፡ ፡ አሁንም ያዩበታል፡፡ በእኔ እምነት በአስር ሺዎች መስዋዕትነት የተከፈለበት የዚያ ትውልድ የነፃነት፣ የዴሞክራሲና የእኩልነት ጥያቄ ትግል ጨንግፏል፡ ፡ በዚያ ጊዜ የነበረው አፈና፣ ግድያና እስር አሁንም መልኩን ቀይሮ ቀጥሏል፡፡ ልዩነቱ አሁን አፈናውን፣ ግድያውንና እስሩን የሚያካሂደው የአቶ መለስ አገዛዝ ሲሆን በዚያ ጊዜ ደግሞ መንግስቱ ኃ/ ማርያምና ደርግ መሆናቸው ብቻ ነው፡፡
ክቡር ፍ/ቤት የእኔም ሆነ የድርጅቴ የአንድነት ትግል ወቅታዊ ትኩረት አቶ ‹‹ሀ››ን ከስልጣን በማውረድ አቶ ‹‹ለ››ን ወደ ስልጣን ማምጣት አይደለም፡፡ ትግሉ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ መስፈን እንቅፋት የሆኑትን ሀይሎች ሁሉ መለወጥ ነው፡፡ ትግሉ ለብሔራዊ መግባባትና እርቅ በር የዘጋውን አምባገነን ስርዓት ለሰላም፣ ለውይይትና ለእርቅ በሩን እንዲከፍት ማድርግ ነው፡፡ ትግሉ የመንግስትንና የገዥውን ፓርቲ ሥራና ተግባር በመደባለቅ በህዝብ ቢሮክራትና በህዝብ ገንዘብ ፓርቲ እያደራጀ ያለውን ተቋማዊ ሙሰኛ ማስወገድ ነው፡፡ ትግሉ ህዝብ የፈለገውን የፖለቲካ ፓርቲ የመደገፍ ህገ-መንግስታዊ መብትን በመፃረር የተቃዋሚ ድርጅት ጽ/ቤት በሮች ላይ ተቀምጠው የሚወጣውንና የሚገባውን ሰው ሁሉ የሚያስፈራሩ፣ በህዝብ ሀብት እየተዳደሩ ህዝብን የሚያስፈራሩ የመንግስት ደህንነቶችን አትችሉም በቃ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ወቅታዊ የትግሉ ትኩረት ህዝብን ከፍርሃት ቆፈን ነፃ በማውጣት ክቡር ፍ/ቤት፡- እኔም ሆንኩ የኢትዮጵያ ወጣት በአጠቃላይም የኢትዮጵያ ህዝብ የግንቦት ሰባት አባል መሆን ሳያስፈልገን የሻዕቢያም ተላላኪዎች ሳንሆን ለነፃነታችን መታገል እንችላለን፡ ፡ ህዝብን እየጨቆኑ የሚመጣ ልማትም ሆነ እድገት ባርነት ነው ማለት እንችላለን፡፡ የካድሬ ልጅ ጠግቦ ኬክ ኬክ እያገሳ የብዙሃኑን ኢትዮጵያዊ ልጅ ዳቦ መመገብ ያልቻለ ልማትም ሆነ እድገት በአፍንጫችን ይውጣ ማለት እንችላለን፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ተላላኪ ወይም ደግሞ አሸባሪ ሳይሆን ነፃ አውጭም ሳያስፈልገው ለመብቶቹ መታገልና ግፍን ማስወገድ፣ ከጭቆናም ነፃ መውጣት ይችላል፡፡ ራሱን ችሎ በሰላማዊ ትግል አበይት ለውጥ ማምጣት እንዲችል ጭቆና በቃኝ ዘረኝነት አንገሸገሸኝ፣ አቶ መለስ ከጫንቃዬ ይውረዱ ማለት ይችላል፡፡ ይህንሻዕቢያ ሊያቅድለት አይችልም፡፡
ክቡር ፍ/ቤት፡- አሁን በአገዛዙ እየተወሰዱ ያሉት የእስር እርምጃዎች ዋነኛ ምክንያት ሽብር ስለተሞከረ፣ ወይም ስለታቀደ፣ ወይም ደግሞ የሻዕቢያ ተላላኪ ስለተገኘ ሳይሆን ዜጐች ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀም የሚያቀርቧቸውን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች ማዳፈን ነው፡፡ እስሩ ባለ ሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ባለች ሀገራችን ለምን ራበን /ለምን ኑሮ ተወደደ/ ትላላችሁ ነው፡፡ ለምን የነፃነት ጥያቄ ታነሳላችሁ ነው፡፡ የእስሩ ምክንያት ለምን እኔ የምላችሁን ብቻ አትቀበሉም ነው፡፡ ለምን የለውጥ ጥያቄ ታነሳላችሁ ነው፡፡ የእሥሩ ምክንያት በአረብ አገራት የለውጥና የነፃነት ንፋስ ወደ አቶ መለስ አገዛዝም እንዳይመጣ የተወሰደ የመከላከል እርምጃ ነው፡፡
ክቡር ፍ/ቤት፡- በሰላማዊ ፓርቲዎችና በህዝቡ የሚነሱ የዳቦ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ የጥያቄውን ባለቤቶች የማንነታቸው መገለጫ ካልሆኑ የሽብር ድርጊቶች ጋር በማገናኘት በአባትም በእናትም ከማይገናኛቸው ሻቢያ ጋር በማገናኘት /በታሪክ፣ በዓላማና በስልት ከማይገናኛቸው ሻዕቢያ ጋር በማገናኘት በሻዕቢያ ተላላኪነት በመፈረጅ የህዝቡ ቀጥተኛ የለውጥና የነፃነት ጥያቄን ለማዳፈን መሞከር የትክክለኛ አዕምሮ ውጤት ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ እኔ አቶ ናትናኤል መኮንን የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ም/ቤት አባልና መስራች የወረዳ 2 እና 14 ሰብሳቢ /አደራጅ/፣ በሰላማዊ ትግል የማምን የኢትዮጵያ ህዝብ ሲራብ ተርቤ፣ ሲጠማ ተጠምቼ፣ ሲገረፍ ተገርፌ፣ እስሩንም መከራውንም ከህዝቤ ጋር እየተቀበልኩ ለዴሞክራሲና ለነፃነት የሚደረገውን ሰላማዊ ትግል ከሌሎች ሰላማዊ ታጋዮች ጋር በመሆን በፅናት እያካሄድኩ ያለሁ፣ ከችግሩ ባለቤት ከኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍና አጋርነት በስተቀር የማንንም ድጋፍ የማልፈልግና የማንንም ፍላጐት የማላስፈፅም፣ የሀገሬን ጥቅም በምንም ሁኔታ አሳልፌ የማልሰጥ፣ ኃላፊነት የሚሰማኝ፣ ኢትዮጵያዊና የአንድነት አባል ነኝ፡፡ አዎ እኔ የግንቦት ሰባት አባል ሳልሆን የአቶ መለስ ረጅም አገዛዝና ጭቆና በቃኝ ያልኩ የሻዕቢያ ተላላኪ ሳልሆን ለነፃነቴ መታገል የምችል፣ ነፃነቴን እስከ ሞት ድረስ የወደድኩ ኩሩ ኢትዮጵያዊና የአንድነት አባል እንጅ ሽብርተኛ፣ የሻዕቢያ ተላላኪና የግንቦት ሰባት አባል አይደለሁም፡፡ አያቶቼ እንዳስተማሩኝ ኢትዮጵያዊነት የርህራሔ፣ የኩራትና የነፃነት ምልክት እንጅ የጭካኔ፣ የባርነትና የውርደት ምልክት አይደለም፡፡ ስለዚህ የጭካኔ ምልክት የሆነው ሽብር ፈፃሚም አስፈፃሚም አይደለሁም፡፡ ወደፊትም አልሆንም፡፡ በሰላማዊ መንገድ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ የሚደረገውን ትግል ከድርጅቴ ከአንድነት ጋር በመሆን በፅናት የትም፣ መቼም፣ በምንም ሁኔታ ውስጥ ሆኜ እቀጥላለሁ፡፡
አዎ ያለነፃነት መኖር በቃኝ በቃኝ፡፡
ፈጣሪ አገሬ ኢትዮጵያን ጠብቃት
አሜን!!!

1) Source: http://ethioforum.org/?p=10324

Advertisements
This entry was posted in ማህበራዊና ባህል/በአማርኛ, standard. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s