Reporter Interview – Prof. Ephrem Yishak & More

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለቅንጅት ሰዎች የተወሰኑ የሚኒስትርነት ቦታዎችን ለመስጠት ቃል ገብተውልን ነበር››

ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ፣ የአገር ሽማግሌዎች ኅብረት ሊቀመንበር

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዜና ዕረፍት ከተነገረበት ከነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሊያስብል በሚችል ሁኔታ ሐዘናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ በአፍሪካና በዓለም ላይ ያሉ መሪዎችም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት ተከትሎ የሐዘን መግለጫቸውን በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ቆንስላዎቻቸው አማካይነትና በተለያዩ የዜና አውታሮች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች ኅብረትም ነሐሴ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. በሸራተን ሆቴል ለተለየዩ የመገናኛ ብዙኅን የሐዘን መግለጫውን አስተላልፏል፡፡ በዛሬው የቆይታ አምዳችን ላይ እንግዳ ያደረግናቸው የ75 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ የሆኑትን ምሁርና የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች ኅብረት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅን ነው፡፡ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር የተዋወቁበትን ጊዜና እስከ ዕረፍተ ዜናቸው ድረስ የነበራቸውን ግንኙነትና ስለሳቸው ያላቸውን አስተያየት በሚመለከት ታምሩ ጽጌ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡-  ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር መጀመርያ የተገናኛችሁት መቼ ነበር?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- እኔ አሜሪካ አገር ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ አስተምር ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ ውስጥ ማለቴ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ በውጭ አገር የምንኖር ኢትዮጵያውያን ‹‹የፊደል ሠራዊት ማኅበር›› የሚባል ፕሮጀክት መሥርተን እዚህ አገር ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ትምሀርት እንዲማር አድርገናል፡፡ በዚህ ማኅበር ምክንያት የምንገናኘው ኢትዮጵያውያን፣ ስለአገራችን ጦርነት መንስዔና እያደረሰ ስላለው ጉዳት መነጋገር ጀመርን፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ ከ1974 እስከ 1991 ድረስ በአገራችን የነበረው ጦርነት የሚያሳቅቅና የሚያሳዝን ነበር፡፡ ብዙ ሕዝብ አልቋል፡፡ አንድ አሜሪካዊ በጻፈው መጽሐፍ ላይ ‹‹በ100 ዓመታት ውስጥ ከነበረው ጦርነት ትልቁና የከፋው ጦርነት›› ብሎታል፡፡ በዚህ ምክንያት ግራ ገብቶን ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1989 ላይ እነ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም (የኢዲዩ መሥራች)፣ ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴም ደወሉልኝና ‹‹ምነው ዝም አላችሁ? ወገን ከወገኑ ጋር እየተላለቀ ነው፡፡ በረሃብ ወገን እየሞተ ነው፤›› አሉኝ፡፡ በዚህ ምክንያት የረሃብ ኮሚቴ አቋቋምንና ከኒውዮርክ ገንዘብ አሰባሰብን፡፡ ነገር ግን ስናስበው የኢትዮጵያ ችግር ረሃብ አለመሆኑን አወቅን፡፡ ረሃቡ የሚመጣው በዝናብ እጥረት ምክንያት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ችግርና ረሃብ ግን ጦርነት ነበር፡፡ በአገራችን ውኃም ሆነ መሬት ሞልቶናል፡፡ ነገር ግን ወገን ከወገኑ ጋር በሚጣላበት ወቅት ገበሬ መሥራት አይችልም፡፡ የዘራውን ሳይሰበስበው በትኖት ይሸሻል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ራሱም ሆነ ቤተሰቡ ረሃብተኛ ይሆናሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ መፍትሔው ሰላም መፍጠር ብቻ ነው፡፡

በዚህ ምክንያት በፖለቲካ ውስጥ የሌለንበት፣ ነገር ግን በትምህርት ደረጃ የተሻልነውና ስለአገራችን ስንሠራ የነበርነው ሰዎች ተደዋወልንና መመካከር ጀመርን፡፡ ዶ/ር ጥላሁን በየነ (የኤርትራ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት)፣ አቶ ፍስሐ ጽዮን ተክኤ (የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር)፣ ዶ/ር ኃይለ ሥላሴ በላይ (የግብርና ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት)፣ ዶ/ር አህመድ ሙኤል (የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር)፣ ፕሮፌሰር አስቴር መንገሻ (በአሪዞና ዩኒቨርሲቲ የሴት ተማሪዎች ፕሬዚዳንት)፣ ፕሮፌሰር አባይነህ ወርቄ (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ዲን)፣ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (የአፋር ነፃ አውጭ ግንባር ጠበቃ)፣ አቶ ካሳሁን ብስራት (የኢትዮጵያ አስተማሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት) በድምሩ 12 ሆነን አሜሪካን አገር ውስጥ ተሰባስበን ተመካከርን፡፡ በወገናሞች መካከል የሚደረገውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለማስቆም ቆርጠን ተነሳን፡፡ የሽምግልናችንን መጀመርያ ለፖለቲካ መሪዎቹ በሙሉ ማለትም ለአቶ መለስ ዜናዊ፣ ለጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ ለኦነግ መሪዎችና ለሌሎቹም በሙሉ ደብዳቤ ጻፍን፡፡ ፈጥነውና ጥያቄችንን ተቀብለው ምላሽ የሰጡን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ በአካል ባንገናኝም በተነሳንበት ዓላማ ዙሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ በደብዳቤው ተዋወቅን፡፡

ሪፖርተር፡- የደብዳቤው ይዘት ምን ነበር?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- የደብዳቤው ይዘት ወይም የሚለው፣ ‹‹እኛ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ የሆነው ኢትዮጵያውያን አገራችንን የምንወድና ያገለገልን ነን፡፡ አገራችን በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በረሃብ ወድቃ ስናይ በጣም ትልቅ ሐዘን ተሰምቶናል፡፡ እናንተም አገራችሁን እንደምትወዱ እናውቃለን፡፡ በመሆኑም በአገራችን ሰላምና ዕርቅ እንዲፈጠር ስለምንፈልግ ፈቃደኛነታችሁን እንድትገልጹልን እንፈልጋለን፡፡ በቀጣይም በአንድ ቦታ ስብሰባ አድርገን ሁላችሁም እንድትገናኙና እንድትነጋገሩ እንፈልጋለን፤›› የሚል ነው፡፡ የሚገርመውና የሚደንቀው ነገር መጀመርያ መልስ የሰጡን አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ጦር ሜዳ ነበሩ፡፡ ደብዳቤውን እንዴት  አደረሳችሁላቸው?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- ደብዳቤውን የላክንላቸው በፋክስ ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር ደብዳቤውን በጻፍንበት ወቅት እነአቶ መለስ በተለይ በጐንደር በኩል ወደ መሀል ተቃርበው ነበር፡፡ ያም ሆኖ ሰላም ፈላጊ በመሆናቸው የላክነውን ደብዳቤ በማክበር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ደብዳቤው ፋክስ የተደረገው የትና በማን በኩል ነው?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- በሽምግልና ውስጥ የተካተቱትና የተመረጡት ሽማግሌዎች፣ በተለያዩ የሥራ ዘርፍና በዘር ግንኙነት ያላቸው ነበሩ፡፡ ከፖለቲካ ድርጅት ኃላፊዎቹ ጋር ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ሲመረጡም ማን ከማን ጋር ግንኙነት እንዳለው ተጠንቶ ነበር፡፡ እኛ አብረን ስንቀመጥ አበባ ነን፡፡ የምንቀመጠው በአንድ ብርጭቆ ነው፡፡ ብርጭቆው ደግሞ ኢትዮጵያ ናት፡፡ በዚህ መሠረት አንድ ለመሆንና ከልብ ለመሆን የሚያስችለንን ሥራ (ሽምግልና) ለመጀመር ባለን ግንኙነት አማካይነት ደብዳቤውን ፋክስ አደረግነው፡፡ ሁሉም (የፖለቲካ ድርጅት ኃላፊዎች) ጥሩ ምላሽ ሰጡን፡፡ በርቱ ግፉበት ጥሩ ነው የሚል፡፡ ሽማግሌዎች በመሆናችን አክብረውናል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሽማግሌ ሰላምና ክብር ነው፡፡ በደርግ በኩል ግን በቀጥታ ደብዳቤ ተጽፎልን ሳይሆን በአንዳንድ አምባሳደሮች አማካይነት በአፍ ነበር ይሁንታውን የሰጡን፡፡ 

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ፈጣን ምላሽ ከሰጧችሁ በኋላ ምን አደረጋችሁ?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- እሳቸው ፈጣን መልስ በመስጠታቸው አመሰገናቸው፡፡ አደነቅናቸው፡፡ ከደርግ በኩል ግን ምላሽ ባለማግኘታችን ሐሳባችን እንደፈለግነው ሊሄድልን አልቻለም ነበር፡፡ በዚህ መሀል ቦሽዊትና ጐሄል የሚባሉ አሜሪካኖችና ሌሎች ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ በዚህ ጊዜ ለጊዜው እኛ መንቀሳቀስ አቆምንና ሥራችን ወደ ፊት እንደሚቀጥል ለደርግ እንዲነግሩልን መልዕክት ላክን፡፡ እዚህ ሲደርሱ ግን የሆነው ሌላ ነው፡፡ ውስጠ ነገሩ ብዙ ስለሆነ መዘርዘር አያስፈልግም፡፡  የደርግን ደብዳቤ በመጠባበቅ ላይ እያለን ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በድጋሚ ሌላ ደብዳቤ መጣልን፡፡ 

ሪፖርተር፡- ምን የሚል ደብዳቤ?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- በወቅቱ እነሱ እያሸነፉ ነበር፡፡ ይኼም ቢሆን ግን ‹‹አሸናፊ ነኝና ዕርቅ አልፈልግም›› አላሉም፡፡ እኛ ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶች ስዊስ ላይ ለመሰብሰብ ያሰብነው እ.ኤ.አ በሰኔ ወር 1989 ላይ ነበር፡፡ በደብዳቤያቸው ‹‹ስብሰባችሁን ሰኔ ከማድረግ ይልቅ ወደ ግንቦት ቀረብ አድርጉት›› ብለው ጻፉልን፡፡ ቆም ብዬ ስለሁለተኛው ደብዳቤያቸው ሳስብ፣ ሁሉም ነገር በሰላም እንዲያልቅ የነበራቸው ፍላጐትን ያሳየኛል፡፡ ጦርነት ከቀጠለ ብዙ ሰው እንደሚያልቅ ገብቷቸዋል፡፡ በመሀል ግን አሜሪካኖቹ ለንደን ላይ ስብሰባ አደረጉና እኛንም ጋበዙን፡፡ እኛ ሽማግሌዎቹ ግን በራሳችን መፍትሔ ማድረግ እንዳለብን ስለምናምን ስብሰባው ላይ አልተገኘንም፡፡ እኔና ዶ/ር ኃይለ ሥላሴ ግን ለንደን ሄደን ስለነበር ማታ ማታ የፖለቲካ ድርጅቶቹ መሪዎች ይመጡና የነበረውን ሁሉ ይነግሩን ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ በደብዳቤ ብቻ እንገናኝ የነበሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ለመጀመርያ ጊዜ በአካል ያገኘኋቸው ለንደን በተካሄደው ስብሰባ ላይ በተገኙበት ወቅት ነበር፡፡ ግን የለንደኑ ስብሰባ ውጤት ሳያመጣ እነ አቶ መለስ አገሪቱን ተቆጣጠሩ፡፡ የእኛ ፍላጐት ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ከተገናኙና ከተወያዩ በኋላ የሽግግር መንግሥት በጋራ እንዲያቋቁሙ ነበር፡፡ ያ ግን አልሆነም፡፡

ሪፖርተር፡- ጦርነቱ አበቃና እነ አቶ መለስ አዲስ አበባ ገቡ፡፡ ከዚያ በኋላ የእናንተ ሥራ በምን መልኩ ቀጠለ?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ተጋበዙና አዲስ አበባ ላይ ስብሰባ አደረጉ፡፡ በወቅቱ የበጀት ችግር ስለነበር (ባንኮች በሙሉ ተዘግተው ስለነበር እኛ ከሽማግሌዎች ማኅበር) 35 ሺሕ ዶላር ወጭ አድርገን በአፍሪካ አዳራሽ ስብሰባው ተካሄደ፡፡ ከመኢሶንና ለጊዜው ከማላስታውሰው አንድ ፓርቲ ውጭ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ተገኝተው ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ከአፍሪካ አዳራሽ ስብሰባ በኋላ ያገኟቸው ነበር?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- የአፍሪካ አዳራሽ ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት አግኝተናቸዋል፡፡ ከዚያም በኋላም ተገናኝተናል፡፡ በመሀላችን የነበረው ድልድይ እየጠነከረ መጣ፡፡ በወቅቱ ተደርጐ የነበረው ስብሰባ እጅግ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ቀና አስተሳሰብና ሰላም ፈላጊነት የጀመርነው የሽምግልና ሥራ ባንድም በሌላም ተሳክቶ ነበር፡፡ በመቀጠልም እ.ኤ.አ በ1990 አዲስ አበባ ውስጥ ቢሮ ከፈትን፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በዚያን ወቅት የነበራቸው የአመራር ብቃት እንዴት ነበር?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- በእውነት ለመናገር በወቅቱ በመሪነታቸው ዕውቅናን አግኝተዋል፡፡ በጦርነቱ ውስጥም ብዙ በመቆየታቸው ልምድ ያገኙ ይመስለኛል፡፡ አንድ ሰው ሊገመት የሚችለው የሚሰማውን አዳምጦ መልስ ሲሰጥና ማመዛዘን ሲችል ነው፡፡ እሳቸውም በዚህ በኩል ምንም ጉድለት አልነበረባቸውም፡፡ አቶ መለስ የሰላምና የዕርቅ ሰው ናቸው፡፡ ሰላም ጥሩ ነው፡፡ ዕርቅ ግን ሰዎችን የሚያቀራርብና ከልብ የመነጨ የዕውነት መቀበል ነው፡፡ እሳቸውም ይኼንን ፈላጊ ናቸው፡፡ ከአቶ መለስ ጋር በተደጋጋሚ መገናኘት ከጀመርንና አዲስ አበባ ውስጥ ቢሮ ከከፈትን በኋላ፣ እኔ ቶሎ ቶሎ እመጣ ነበር፡፡ በምመጣበት ጊዜ ለእስረኞች ምህረት እንዲያደርጉ ጠየቅኳቸው፡፡ ተቀበሉኝ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ ደብዳቤ እጽፍላቸዋለሁ፡፡ አሁንም መጨረሻ ላይ የተገናኘን ጊዜ ስለ እስረኞች አነጋግሬያቸው ጊዜው ሲደርስ ብለውኝ ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው በሞት ተነጠቅን፡፡ አሁን የመጣሁት ሞታቸውን ለመረዳት ሳይሆን ለማነጋገር ነበር፡፡ ለአዲስ ዓመት ይምጡ ብለውኝ ነበር፡፡ መጥቼ ሞታቸውን ሰማሁ፡፡ አንዳንድ ሰዎች እሳቸውን በደንብ ሳያውቋቸው መጥፎ ቃል ይጥሉባቸዋል፡፡ እሳቸው ግን እነሱ እንደሚሏቸው ዓይነት ሳይሆኑ አዳማጭና ሰሚ ናቸው፡፡ ምክር ይቀበላሉ፡፡ እኛ ተራ ሰዎች ነን፡፡ ነገር ግን ፍላጐታችን ከአገር ፍቅር የመነጨ መሆኑን ተረድተውናል፡፡ በመሆኑም ላለፉት በርካታ ዓመታት በየዓመቱ በድምሩ ከ80 ሺሕ በላይ እስረኞችን ለቀዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) እ.ኤ.አ በ1991 ላይ ከሌሎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አዲስ አበባ በተደረገው ስብሰባ ላይ ውይይት ካደረገና የተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላ ወጥቷል፡፡ እናንተ ምክንያቱን ጠይቃችሁ ለማስማማት ያደረጋችሁት ጥረት ነበር?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- የእኔ ዋና ዓላማ የፖለቲካ እርቅ እንዲፈጠር፣ እስረኞች እንዲፈቱና ሰላም እንዲሰፍን ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በጥልቀት ጉዳዩን አላውቅም፡፡ ምክንያቱም ፖለቲከኛ ስላልሆኩኝ ነው፡፡ ሌሎቹን ግን መጠየቅ ይቻላል፡፡ እኔ ግን በጥልቀት አለማወቄ ስጠየቅ ያሳፍረኛል፡፡

ሪፖርተር፡-  የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ችግሩ እንደሚፈጠር እርስዎ እንደሚያውቁ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስና ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተወያይተዋል ይባላል፡፡

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- እ.ኤ.አ በ1997 እስረኞችን ለማስፈታት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ለማነጋገር መጥቼ ነበር፡፡ ዶ/ር ጥላሁን የሚባሉት ጓደኛዬ (የሽማግሌዎቹ አባል) በኤርትራ በኩል መጥተው አዲስ አበባ ተገናኘንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን በጋራ አገኘናቸው፡፡ ስንወያይ ዶ/ር ጥላሁን በባድመ በኩል ችግር እንዳለ ገለጹላቸው፡፡ በሰላም መፍታት እንዳለብንም ተማምነን ተለያየን፡፡ ስምምነቱ ሳይደረግ ወይም ሳይጀመር ከሦስት ወራት በኋላ ጦርነቱ ተጀመረ፡፡ እኔ ወዲያውኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስና ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ደብዳቤ ጻፍኩኝ፡፡ እነሱም የእኛን የሽማግሌዎቹን ጥያቄ አከበሩ፡፡ በእኛም እንደሚያምኑ ገለጹልን፡፡ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ምክንያት አቶ መለስን ለማነጋገር ሦስት ጊዜ መጣን፡፡ አቶ ኢሳያስንም እንዲሁ፡፡ የበጀት ችግር ስለነበረብን ብቻዬን መመላለስ ጀመርኩኝ፡፡ በዚህ ጊዜ ከእሳቸው ጋር በብዛት የመገናኘቱ ዕድል ገጥሞኛል፡፡ ስለጦርነቱ መቆም ስንነጋገር ግን መጀመርያ ከባድመ መልቀቅ እንዳለባቸው ይናገሩ ነበር፡፡ በእነኛ በኩል ደግሞ መጀመርያ መስማማት አለብን የሚል አቋም ተይዞ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ 2000 ላይ ጦርነቱ አበቃ፡፡ በእኛ ሽምግልና ላይ የውጭ ሰዎች ማለትም እነ አልጄሪያ ገቡና መሆን የማይገባው ነገር ሆነ፡፡ 

ሪፖርተር፡- በኢትዮ ኤርትራ ሽምግልና ላይ እስከ መጨረሻው ነበራችሁ?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- ከሁለቱም መሪዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበረን፡፡ የአገር ሽማግሌዎችን ሁለቱም ያምኑባቸዋል፡፡ ያበላሹብን የውጭ አገር ሰዎች ናቸው፡፡ ጣልቃ መግባት ስለሚወዱ አልጄሪያ ጣልቃ ገብቶ ስብሰባው አልጀርስ ተደረገ፡፡ በታዛቢነት እንድንገኝ ቢጠሩንም አልሄድንም፡፡ ምክንያቱም እኔ መሄድ የምፈልገው ኢትዮጵያና ኤርትራ ሲነጋገሩ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ሦስተኛ ወገን ነገሮችን ያበላሻል፡፡ ተበላሸ፡፡

ሪፖርተር፡- በአልጀርሱ ስምምነት ላይ በውጭ አገሮች ጣልቃ ገብነት ተበላሽቷል የሚሉት ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- እኔ የማምነው አንድ ነገር አለ፡፡ ብዙ ጊዜ በሰዎች መካከል ስምምነት የሚፈጠረው በነገሩ ላይ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ሰላም ተፈጥሯል በማለት በር ዘግቶ መቀመጥ ስምምነት አይደለም፡፡ አብሮ ቡና መጠጣትና መነጋገር ሲቻልና ከልብ ሲሆን ነው ስምምነት፡፡ እኔ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ ላይና ኖርዌይ ውስጥ ያደረኩት ንግግር አለ፡፡ የውጭ አገር አስማሚዎች ሁልጊዜ ከአዕምሮ ውስጥ ያለውን ነገር ለማወቅ ነው የሚሄዱት፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ሽማግሌዎች ግን ለማወቅ የምንሄደው የልብን አስተሳሰብ ነው፡፡ የሰው እርቅ ደግሞ ከልብ ካልሆነ እርቅ አይደለም፡፡ የእኛ ፍላጐት የኢትዮጵያና የኤርትራ እርቅ ከልብ እንዲሆን ነበር፤ ይኼ አልሆነም፡፡ አስታራቂዎቹ ማድረግ ስለማይችሉና ልምዱም ስለሌላቸው ነው፡፡ የልብን በር መክፈት ቀላል አይደለም፡፡ እኛ በትህትና፣ በፍቅርና በመንፈሳዊ መንገድ ነው የምንሄደው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የ1997 ዓ.ም. ምርጫን ተከትሎ በተፈጠረው አለመግባባት በርካታ የቅንጅት አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች መታሰራቸው ይታወሳል፡፡ ይኼንን ተከትሎ የአገር ሽማግሌዎች ባደረጋችሁት የማግባባት ሥራ ከእስር ተፈትተዋል፡፡ በሽምግልናችሁ ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር ባደረጋችሁት ውይይት የእሳቸው አቀባበልና ምላሻቸው እንዴት ነበር?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- እኛ ግንኙነታችንን አቋርጠን አናውቅም፡፡ እንገናኝ ነበር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በየዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል የገቡልን የእስረኛ መፍታት ፕሮግራም ነበር፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ተፈጥረው በነበሩ አለመግባባቶች ዙሪያ የተገኙ መስማማቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው መከታተልም ነበር፡፡ ምርጫው ከመደረጉ በፊትም በጥሩ ሁኔታ እንዲካሄድ እንመካከር ነበር፡፡ ከቅንጅትንም ሆነ ከኢሕአዴግ አመራሮች ጋር እየተገናኘን እንወያይና እንመካከር ነበር፡፡ እንመክራቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን በምርጫው ምክንያት ችግር ተፈጠረ፡፡ እኔ እዚህ ባልኖርም እዚህ ያሉትን ሽማግሌዎች ደውዬ ችግሩ እንዲቆም ጥረት እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፌ ነበር፡፡ የተለያዩ ድርጅቶችም ሽምግልና ጀምረው ነበር፡፡ እኔ በመስከረም ወር 1998 ዓ.ም. መጣሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በጥሩ ሁኔታ ተቀበሉኝ፡፡ ‹‹አዲስ አበባ ላይ ቅንጅት አሸንፏል፡፡ እኛ ደግሞ በሌላው ቦታ አሸንፈናል፡፡ እነሱ አዲስ አበባን ያስተዳድሩ፤ እኛ ደግሞ አገር እንመራለን ምከሯቸው፡፡ ወደ ፓርላማ ይግቡና ሌላውን ነገር ሁሉ ፓርላማ ውስጥ እንጨርሳለን፤›› አሉኝ፡፡ አቶ መለስ ለመወያየት በራቸውን ወለል አድርገው ከፍተው ነበር፡፡ ብዙ ነገር ተወያይተንም ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለቅንጅት ሰዎች የተወሰኑ የሚኒስትርነት ቦታዎችን ለመስጠት ቃል ገብተውልን ነበር፡፡ ችግሮች ሁሉ በሰላም እንዲጠናቀቁ ይፈልጉ ነበር፡፡ የቅንጅትንም ሰዎች ኢንጂነር ኃይሉ ሻውልን፣ ዶ/ር ብርሃኑን፣ ዶ/ር ያዕቆብንና ሌሎችንም አግኝተን ከተነጋገርን በኋላ በሰላም የሚያልቅ መስሎኝ ወደ አሜሪካ ተመለስኩኝ፡፡

በመሀል ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ደብዳቤ ጻፉልኝ፡፡ ሁለትና ሦስት ጊዜ ጽፈውልኛል፡፡ ደብዳቤያቸው ‹‹ምከሯቸው እነሱ አዲስ አበባን ያስተዳድሩ፡፡ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እኛም ኃላፊነታችን ከባድ ነውና አገር እናስተዳድር፤›› የሚል ነበር፡፡ ለቅንጅት ሰዎች የእሳቸውን ደብዳቤ ጠቅሼ ጻፍኩላቸው፡፡ በሁለተኛው ደብዳቤ ቅንጅቶች አለመስማማታቸውን ገለጹልኝ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእውነት አምባገነን አይደሉም፤ ሰላም ፈላጊ ናቸው፡፡ ባለመስማማታቸው ግጭት ተፈጥሮ ብዙ ሰዎች ሞቱ፡፡ የቅንጅት ሰዎችም ታሰሩ፡፡ እኔ ወዲያው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሄድኩኝ፡፡ የነበረውን ነገር ሁሉ ከተነጋገርን በኋላ እስር ቤት ሄጄ እንዳነጋግራቸው እንዲፈቀድልኝ ስጠይቃቸው ተፈቀደልኝ፡፡ ፖሊስ ጣቢያ እያሉ ሁሉንም አነጋገርኳቸው፡፡ ክስ ሳይመሠረት እንዲስማሙ ሽማግሌዎች ስንጥር አቶ መለስ ፈቃደኛ ነበሩ፡፡ ቅንጅቶቹ ባለመስማማታቸው ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት አመራ፡፡  ከዚያ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ጉዳዩ ከእጄ ወጥቷል፤ ፍርድ ቤት በያዘው ጉዳይ ጣልቃ አልገባም፤›› አሉኝ፡፡ እስከሚፈረድባቸው ጠበቅን፡፡ አንድ መግለጽ የማልፈልገው ነገር አለ፡፡ ወደፊት የምናገረውና ጠቃሚ የሆነ ነገር አለ፡፡ ብዙ ጊዜ የቅንጅት ሰዎች ‹‹ለምን አትናገርም?›› የሚሉት፡፡ መንግሥት ክሱን ለመተው ፈልጐ ነበር፡፡ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ሳይሄድ፡፡ እሳቸው በር ከፈቱ፡፡ ሰላም እንዲወርድ፡፡ ከዚህ በላይ ምን ያድርጉ?

ከመጀመርያው ጀምሮ እስካሁን ድረስ አቶ መለስ ለሰላምና ለእርቅ ያላቸው ፍላጐት ከፍተኛ ነበር፡፡ አሁን የሚያስለቅሰኝና የሚያሳዝነኝ ይኼ ነው፡፡ የእኔ ሐዘን ለእሳቸው ብቻ አይደለም፡፡ ለኢትዮጵያውያንም ለአገሬም ነው፡፡ ለኢትዮጵያ የነበራቸው ህልም ቅን ነበር፡፡ ምክር ሰሚ ነበሩ፡፡ ስህተት ሲፈጠርም ይቅርታ የሚጠይቁ ነበሩ፡፡ 

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ በመነጋገር ላይ የነበራችሁበት የማስማማት ጉዳይ ምን ነበር?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- በእጃችን ላይ የነበረው ብዙ ነገር ነው፡፡ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ አልገባም፡፡ በኦጋዴን ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት ነበር፡፡ ስለኦነግ፣ ስለኤርትራ፣ ስለእስረኞችና ስለሃይማኖት ጉዳዮች የተወያየንበትና መፍትሔ ለመስጠት ዳር ላይ የደረስንበት ሁኔታ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በኤርትራ ጉዳይ ላይ ብዙ ተነጋግራችሁ ነበር?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- እጅግ በጣም ብዙ ብዙ፡፡ እሳቸውም መፍትሔ ይፈልጉ ነበር፡፡ እኛም ብዙ ነገር አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- ሁለቱን መሪዎች ለማነጋገር ሞክራችሁ ነበር?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- እንዴ ይኖራል እንጂ፡፡ ይቅርታ አድርግልኝና አንዳንድ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ መግባት ጥሩ አይደለም፡፡ ለማጠቃለል ያህል በእኛ በሽማግሌዎች በኩል ቀዳዳ እንዳይኖር በሁሉም ቦታ ለመድፈን እየጣርን ነበር፡፡ ዋናው ነገር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለዚህ ጉዳይ ሁልጊዜ ዝግጁ ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ክረምት ሊፈቱላችሁ ቃል የገቡት ስንት እስረኞችንና በምን ጉዳይ የተፈረደባቸውን ነው?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- እኔ ከሦስት ወራት በፊት ሳገኛቸው ጠይቄያቸው፣ ‹‹እሱማ የተለመደ ነገር ነው፤ ቀኑ ሲደርስ ና፤›› ብለውኝ ስለነበር ነው ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. የመጣሁት፡፡ ቁጥሩ ባይታወቅም መፍታታቸውማ ልምድ ሆኗል፡፡ ቃላቸውን የሚጠብቁና ቁምነገረኛ ሰው ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መታመማቸውን ሰምተው ነበር?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- መታመማቸውን የሰማሁት ከሁለት ወር በፊት ነው፡፡ ነገር ግን አላመንኩም ነበር፡፡ ምክንያቱም ሁልጊዜ ሳገኛቸው ጤነኛ ሰው ናቸው፡፡ በቅርቡ በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ላይ አግኝቻቸው ጤነኛ ነበሩ፡፡ ከዚያ በኋላም በደብዳቤ ተገናኝተናል፡፡

ሪፖርተር፡- መታመማቸውን ሲሰሙ ጠይቀዋቸዋል?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- በደንብ እንጂ፡፡ ሄጄ ልጠይቃቸውም ፈልጌ ነበር፡፡ ተሽሎአቸዋል ስለተባለ ቆየሁ፡፡ እንደገናም ሄጄ ለመጠየቅ ፈልጌ ነበር፣ በተመሳሳይ ተሽሏቸዋል ተባልኩኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ማረፋቸውን የሰሙት የት ሆነው ነው?

ፕሮፌሰር ኤፍሬም፡- የመጣሁት ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ነው፡፡ የመጣሁትም እሳቸው እስረኞች ይፈታሉ ብለው በሰጡኝ ተስፋ መሠረት ነው፡፡ ተሽሏቸዋል ሰሞኑን ይመጣሉ ስለተባልኩኝ እንደመጡ ለመገናኘት ነበር የመጣሁት፡፡ ነገር ግን በመጣሁ በማግስቱ ጠዋት አንድ ወዳጄ ደውሎ ‹‹እስቲ ራዲዮ አዳምጥ፤ ስለ አቶ መለስ አስደንጋጭ ወሬ አለ፤›› አለኝ፡፡ እሳቸውማ ተሽሏቸዋል፤ ይመጣሉ አልኩት፡፡ ‹‹ግዴለም አዳምጥ›› አለኝ፡፡ ቴሌቪዥን ስከፍት ቴሌቪዥኑ ዝም ብሎ የእሳቸውን ምስል ብቻ ያሳያል፡፡ ከተወሰነ ደቂቃ በኋላ ተነገረ፡፡ የሆነውን ሁሉ ማመን ቢያቅተኝም ማልቀሴን ቀጠልኩኝ፡፡ ጥልቅ የሆነ ሐዘን ተሰምቶኛል፡፡ አቶ መለስ ዋናው ምኞታቸው የጀመሩት ሥራ እንዲፈጸም ነበር፡፡ ይኼንን ምኞት ይዘን ሁላችንም ሥራችንን እንቀጥላለን፡፡ ወደፊት በኢትዮጵያ ከነበሩት መሪዎች ሁሉ አንዱና ዋናው ተብለው እንደሚጠሩ እምነቴ ነው፡፡ ታሪካቸው እንዲፀና ሁላችንም ጅምሮቻቸውን ተከትለን ተፈጻሚ እንዲሆን መጣር አለብን፡፡ ቤተሰቦቻቸውና የኢትዮጵያ ሕዝብ የደረሰባቸውን ጥልቅ ሐዘን ችለው፣ የእሳቸውን ጅምሮች ከዳር ማድረስ አለባቸው፤ አለብን፡፡

**************************************

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ዕረፍት አስመልክቶ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የሰጡት አስተያየት

በመገናኛ ብዙኅን የሰማሁት ነገር እጅግ ልብ የሚነካና የሚያሳዝን ነው፡፡ የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ትልቅ ራዕይና አቅም የነበራቸው መሪ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ይኼ ነው የማይባል ጊዜያቸውን መስዋዕት አድርገው፣ አምባገነኑን የደርግ ሥርዓትን መክቶ ማሸነፍ የቻለ ፓርቲ መመሥረት የቻሉ ግለሰብ ናቸው፡፡

ከዚያም በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ነው የማይባል የፖለቲካና የኢኮኖሚ መነቃነቅን የፈጠረ አቅም የነበራቸው ግለሰብ ነበሩ፡፡ ወደፊትም በኢትዮጵያ ውስጥ ረጅም ርቀትን ለመሄድ የሚያስችል አቅም የነበራቸው ግለሰብ ናቸው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ለኢትዮጵያ ካቀዱትና ይዘውት ከተነሱት ዓላማ አኳያ መታጣታቸው እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ በተረፈ እንደ አባት ደግሞ ለቤተሰቦቻቸው እጅግ ትልቅ እጦት ነው፡፡ ለአፍሪካ ማኅበረሰብም አፍሪካን በማስተሳሰርና አንድነትን በማምጣት፣ በልማት መስመር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ቀላል የማይባል ሚና የተጫወቱ ግለሰብ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ስናያቸው እንደ አገር መሪ ይዘውትና ሰንቀውት የተነሱት ነገር ረጅም ርቀት የሚወስደን መሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ወደፊትም ቢሆን በጀመሩት ነገር ላይ ተጨማሪ ሥራ ለመሥራት አቅም የነበራቸው ግለሰብ ነበሩ፡፡ እስከዛሬ ድረስ የሰበሰቡት ዕውቀት፣ ያከማቹት ግንዛቤና ተሞክሮ ወደሚቀጥለው ኃይል ተላልፎ አለማየትም ትልቅ እጦት ነው፡፡ በቀጣይ የሚጠበቀው ነገር ከኢሕአዴግ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ በሰፈረው መሠረት ኢሕአዴግ የሥልጣን ሽግግሩን በአግባቡ መወጣት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ፣ በማያሻማና በሚታይ ሁኔታ መሆን አለበት እላለሁ፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ አገርን በማልማትና በማሳደግ ሒደት ውስጥ ቀዳዳ እንዳይኖረው እመኛለሁ፡፡ ተቀራርቦና ተቻችሎ ለመሄድ ብዙ መሥራት ይኖርበታል፡፡ የተፈጠረው ነገር አሳዛኝ ቢሆንም ቆም ብለንና ወደ ኋላ መለስ ብለን እንድናይ፣ እንድናስብና እንድናጠነጥን ያስገድዳል፡፡ ሁላችንም ለአገራችን ቀናኢዎች ነን፡፡ በዕድገቷና በልማቷ ላይ የራሳችን አስተሳሰብ አለን፡፡ ይኼንን ሁሉ ተጋርተን ይህችን አገር ሉዓላዊነቷንና አንድነቷን አስጠብቀን መቀጠል የምንችልበት ዕድል እንዲኖር ነው ምኞቴ፡፡ በምንም ዓይነት ውስጣዊ ግጭትና አለመስማማቶች ቢኖሩ ቅድሚያ ለሕዝቡ ሊሰጥ የሚገባው አክብሮትና ትኩረት መኖር አለበት፡፡ ከዚህ አኳያ ኢሕአዴግ ሥራውን ሠርቶ መገኘት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡

የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ

———————- //——————-

እንደማንኛውም ፍጡርና ሰው በመሞታቸው አዝኛለሁ፡፡ እኔና እሳቸው በትግል ወቅትም አብረን ብዙ ጊዜ ስለነበርን ሕይወታቸው ማለፉ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ ያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ወስጥ ደግሞ በሚቀጥለው ጊዜ እሳቸው ከነበሩበት ጊዜ የተሻለ መግባባትና ነፃነት እንዲፈጠር ፍላጐቴ ነው፡፡ የተሻለ ነገር እንዲኖር በተለይ ፓርቲያቸው በጥብቅ እንዲያስብበት እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ጊዜያት ብዙ ብዙ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ የነፃነትና የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ነበሩ፡፡ የታሰሩ ሰዎች የሚፈቱበትና በአገሪቱ ውስጥ በአጠቃላይ መግባባት የሚፈጠርበት ሁኔታ መኖር አለበት የሚል አስተሳሰብ አለኝ፡፡ ማንም ቢሆን ሕይወቱ እንዲያልፍ ወይም እንዲሞት አልመኝም፡፡ እንኳን አብሮ ብዙ የሠራ ሰው ቀርቶ ማንም ሰው ሲሞት ሐዘን ይሰማኛል፡፡ እሳቸው ደግሞ በትግልም ወቅት አብረን ነበርን፤ ላለፉት አሥር ዓመታት ብንለያይም፡፡ በተለይ በትግል ወቅት በነበርንበት ጊዜ በነበረው ሁኔታ የሚሰማኝ ነገር አለ፡፡

የአረና ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ገብሩ አሥራት

 

———————- //——————-

እኔ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአገራችን ባህል ሰው እንዲህ ዓይነት ነገር ሲገጥመው ነፍሱን ይማረው እላለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ጠዋት (ትናንትና ማለዳ) ስሰማ ደንግጫለሁ፡፡ ነገር ግን አገሪቷ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመፍጠር እጅግ አጣብቂኝ የሆነ ነገር ውስጥ ስለገባች፣ የተሻለች ኢትዮጵያን በጋራ ለመፍጠር ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ እንዲኖር አጋጣሚውን እንዲጠቀም ገዥውን ፓርቲ አደራ እላለሁ፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና
———————- //——————-

በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መሞት አዝኛለሁ፡፡ ሰው ናቸውና እንደ ሰው መታመምም፣ መሞትም እንደሚኖር አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ውስጥ አስተምረውት ሊያልፉ ይገባል ብዬ የማስባቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ሥልጣንን በሞት ሳይሆን በፈቃደኝነት ለቆና ሲቪል ሆኖ ያለአጃቢ ከሕዝብ ጋር መንቀሳቀስና የመሳሰሉ ነገሮችን፡፡  በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ የሚኖረው ሕዝብ ምን ዓይነት ኑሮ እየኖር እንደሆነ መረጃ ከሚያቀርቡላቸው ሹማምንት ውጭ በራሳቸው እይታ ካዩ በኋላ የሚኖራቸው ምላሽ ቢታይ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ በሞተ ሰው ላይ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ማለት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ሳይሞቱ ቢሆን ኖሮ ብዙ ነገር መማማር ይቻል ነበር፡፡ በሕይወት እያሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምባገነን፣ ጨካኝ፣ ወዘተ በማለት ብዙ ኃይለ ቃል ተጠቅመን ገልጸናቸው ይሆናል፡፡ አሁን በሞተ ሰው ላይ ምንም ማለት አስፈላጊም አይደለም፡፡ አይቻልምም፡፡ ከዚህ በኋላ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለው ነገር ታሪክ የሚሆንና ታሪክ የሚፈርደው ጉዳይ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ፓርቲያቸው የሚወስዳቸውን አቋሞች በማየት የምንለው ነገር ይሆናል፡፡ አሁን ሹማምንቱ ከሚሰጧቸው መግለጫዎችና ንግግሮች የምረዳው፣ ምናልባትም ፓርቲውን የሚያስገምተው ነው እላለሁ፡፡ ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስተሳሰብ፣ እይታና ሌሎች ነገሮችን ይዘን እንቀጥላለን›› ሲባል፣ ‹‹ፓርቲው የአንድ ሰው ነበር?›› የሚለውን ነው የሚያሳየው፡፡ ይኼ ትንሽ ኢሕአዴግን እንደ ገዥ ፓርቲ ያስገምተዋል፡፡ በሕይወት ዘመናቸው የበላይነት እንደነበራቸው ይታወቃል፡፡ መሪ ሆኖ የሚመጣው ሰው የራሱን እይታ ይዞ የሚመራበት ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ ለምሳሌ የእኔን መኪና እኔ ስነዳውና አንተ ስትነዳው ይለያያል፡፡ እስከምትለማመደው ብቻ አይደለም፡፡ የአነዳድ ሁኔታው ሁሉ ነው የሚለያየው፡፡ ስለዚህ ለሚቀጥለው መሪ መብት ስትሰጠው ‹‹በፈለግኩት አቅጣጫ ነው የምትመራኝ›› ካልከው የፓርቲውን ደረጃ ያወርደዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ የመሪነት ሥልጣን የሚይዘው ሰው የሚመራበትን ሁኔታ ራሱ መምረጥ ይኖርበታል፡፡ የሚመራበትን ሁኔታ በፓርቲ ማዕቀፍ ውስጥ አስገብቶ መስጠት የሚመራውን ሰው መናቅ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስላሉ አይደለም በሰላምና በፍቅር የሚኖሩት፡፡ አሁንም በሰላም መኖራቸው ይቀጥላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ‹‹ታመዋልና ምን እንሆናለን?›› ሲሉ ምንም አንሆንም ነው ያልነው፡፡ አሁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም አይሆንም፡፡ ግን ደግሞ ምንም የማይሆኑ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥላ ጠብቀው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ካሉ ቢፈሩና ቢሰጉ ተገቢ ነው፡፡ የሚያስፈራቸውና የሚያሰጋቸው የሠሩት ሥራ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም፡፡ መልካም እንቅልፍ ለመተኛት ጥሩ ሥራ መሥራት አለብህ፡፡

የመድረክ ፓርቲ ብቸኛው የፓርላማ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ

———————- //——————-

ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ከ1983 ዓ.ም. እስከ 1993 ዓ.ም. ለአሥር ዓመታት አብረን ሠርተናል፡፡ ከዚያ በኋላ አንድና ሁለት ጊዜ እንጂ ብዙም አልተገናኘንም፡፡ በእሳቸው አመራርና አካሄድ የማልስማማ ቢሆንም አደንቃቸው ነበር፡፡ አሁንም አደንቃቸዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ጐበዝ ናቸው፡፡ ብዙ ያነባሉ፡፡ ብቃታቸውን እኔ በማስበው መንገድ ለአገሪቱ በጥቅም ላይ አውለዋል ወይስ አላዋሉም? ለአገሪቱ ጠቃሚ ነበር ወይስ አልነበረም? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ በጉብዝናቸው የማደንቃቸው ሰው ናቸው፡፡ ይሠራሉ፡፡ እንደሰው ማረፋቸው (መሞታቸው) በጣም ያሳዝነኛል፡፡ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወገኖቻቸውና ለጓደኞቻቸው እግዚአብሔር እንዲያጠናቸው እመኛለሁ፡፡ መደበቁ ትክክል እንዳልሆነና የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 12 ድንጋጌ መጣሱን መግለጽ እወዳለሁ፡፡ ታመዋል ከተባለ 50 ቀናት አልፈዋል፡፡ አገሪቱን 21 ዓመታት ያስተዳደሩ በመሆናቸው፣ ለሕዝቡ በየቀኑ ስለሳቸው እያንዳንዱ ጉዳይ መገለጽ ነበረበት፡፡

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት) ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ

———————- //——————-

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መሞታቸውን ስሰማ ከልብ ነው ያዘንኩት፡፡ በመሞታቸውም ልጆቻቸውን፣ ባለቤታቸውን፣ ዘመዶቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን እግዚአብሔር ያጥናችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የአመለካከት አቅም ያላቸው ባላንጣ ነበሩ፡፡ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳይ ያሉት ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው፣ ብዙዎቹን ሐሳቦች በራሳቸው አስተሳሰብ ለመግለጽና ለማሳመን አቅም ነበራቸው የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ ሆኖም ግን በአንድ በኩል ወደ ኋላ ዘወር ብዬ ስመለከተው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሥር እንዲሰድና አቅም እንዲኖረው፣ ታማኝነት ያለው የፖለቲካ አቅጣጫ እንዲፈጠር የተለያየ አመለካከት ያላቸው ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲኖሩ የነበራቸው አስተዋጽኦ ደካማ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ቀጣዩ የኢሕአዴግ አመራሮች ለሕዝብ ታማኝነት ያላቸው የተቃዋሚ ፓርቲዎች በማሰባሰብ፣ እኛም ተቃዋሚዎች አገራችን በሰላም ነፃነቷን፣ ክብሯንና ህልውናዋን ጠብቃ ወደፊት እንድትራመድ አስተዋጽኦ እንዲኖረን፣ ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ መድረኩን ማስፋት አለበት፡፡ በሕዝብ ተቀባይነት ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገር ልማትና ዲሞክራሲ እንዲሳተፉ ማድረግ ከገዥው ፓርቲ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት የተሰማኝን ሐዘን በድጋሚ መግለጽ እወዳለሁ፡፡

የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ ተመስገን ዘውዴ

———————- //——————-

እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት አሳዝኖኛል፡፡ ወደፊትም የሰከነና የረጋ አመራር እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች የተከፋ ሰው ሊኖር ስለሚችልና ሐዘንም ሲጨመር ከባድ ነገር ሊሆን ስለሚችል፣ አስተዋይነትና አርቆ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የኢሕአዴግ አመራር ይኼንን በብቃት እንዲወጣ እንፈልጋለን፡፡ አቶ መለስ ከወጣትነት ዕድሜያቸው ጀምሮ በተለይ በሥራ ጥንካሬያቸው እኔም በግሌ ጥሩ ሰው እንደሆኑና ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ሰው እንደሆኑ አምናለሁ፡፡ በሥራዎቻቸውና በሆኑት ጉዳዮች ዙሪያ የሚስማማም የማይስማማም እንዳለ ሆኖ፣ የያዙትን ነገር ይዘው በተከታታይ ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በዓላማቸው ፀንተው መቆየታቸው እንደ አንድ ጥሩ ጐን የሚታይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢሕአዴግ ወደፊት እንደተለመደው የጠቅላይነት አስተሳሰብን ትቶ፣ ኢትዮጵያን የሁሉም አድርጐ ማየትና የማሳተፍ ሰፊ የሆነ የፖለቲካ መድረክ መፍጠር፣ ሌሎች አማራጮችን በመፈለግ ኢትዮጵያውያንን ሊጠቅሙ የሚችሉ ትላልቅ ሰዎችን ማሳተፍ አለበት፡፡ ትልቅ አገርና ትልቅ መሪ ማለት ሌሎቹም እንዲበቁ ማድረግ ስለሆነ፣ የሌሎቹም ችሎታ እንዲወጣ በማድረግ በሳል አመራር እንዲኖር ማድረግ አለበት፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት

Advertisements
This entry was posted in Social & Cultural, standard. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s